የልብ ቀዶ ህክምና ለማግኘት ከ10 እስከ 15 ዓመት የሚጠብቁ ታካሚዎች ስለመኖራቸዉም ሰምተናል፡፡
በአሁኑ ሰዓት 8ሺህ ታካሚዎች የልብ ህክምና ለማግኘት በማዕከሉ ዉስጥ ወረፋ እየጠበቁ መሆናቸዉን የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግሯል፡፡
ከእነዚህ ታካሚዎች ዉስጥ አብዛኞቹ ህጻናት ስለመሆናቸዉም ነዉ የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሚክሎል መንግስቱ የተናገሩት፡፡
በአላቂ ዕቃዎች አለመኖር ምክንያት ከህጻንነታቸዉ ጀምሮ ወረፋ እየጠበቁ አሁን ላይ አዋቂ ዕድሜ ደረጃ ላይ የደረሱ ልጆች ስለመኖራቸዉም ነግረዉናል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሳምንት ቢያንስ ለ4 ታካሚዎች የቀዶ ህክምና ይሰጣል ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፤ የተለያዩ ድጋፎች በመገኘታቸዉም ቁጥሩ እዚህ ላይ ሊደርስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ማዕከሉ ባለበት የአላቂ ዕቃዎች ዕጥረት የተነሳ ከዚህ በፊት በሳምንት ለ 2 ታካሚዎች ብቻ የቀዶ ህክምና ይሰጥ እንደነበርም ሜዲካል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በደም ስር ዉስጥ የሚሰጥ ህክምናም በሳምንት ለ4 ታካሚዎች የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዉ፤ይህም በሳምንት ለ8 ታካሚዎች አገልግሎት እንድንሰጥ አስችሎናል ብለዋል፡፡
በዚህ ቁጥር መሰረት በዓመት ወደ 4መቶ አከባቢ ለሚሆኑ ታካሚዎች የልብ ህክምናን መስጠት እንችላለን ነዉ ያሉት፡፡
ማዕከሉ በሙሉ ዓቅሙ መስራት ቢችል በዓመት ከ1ሺህ5መቶ እስከ 2ሺህ ለሚሆኑ ታካሚዎች ህክምና መስጠት ይችላል ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፤ ይህን ለማድረግ ከአላቂ ዕቃዎችም በተጨማሪ የሰዉ ሃይልም የተወሰነ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት እጃችን ላይ ባለዉ ነገር በዓመት ከ6መቶ እስከ 7መቶ ታካሚዎችን የልብ ህክምና ለመስጠት ማቀዳቸዉን ገልጸዉ፤የሚደረጉ ድጋፎች ቢጨምሩ ወደ 1ሺህ ታካሚዎችን ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚቻል ነግረዉናል፡፡
እሰከዳር ግርማ
ህዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም