ሕዳር 10/2016 (አዲስ ዋልታ) የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊያን መፍትሄ ያገኙ ዘንድ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት እንደምታደርግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ፡፡
የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባላትና ቋሚ ኮሚቴዎች በአዲስ አበባ የጋራ ስብሰባቸውን አካሂዷል፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በስብሰባው ላይ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት መመስረት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጓን አስታውሰው በአህጉሪቱ የሚስተዋሉት ችግሮች ተቀርፈው የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የጸና አቋም አላት ብለዋል፡፡
የፓርላማ ዲፕሎማሲ የጋራ ችግሮቻችንን ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የጠቆሙት አፈ-ጉባኤው የፓን አፍሪካ ፓርላማም የቁልፍ ችግሮች መፍቻ በመሆን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳበት አሳስበዋል፡፡
በአፍሪካ አህጉር እየተስተዋሉ ካሉት ችግሮች መካከል ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ድህነት እና የእርስ በእርስ ግጭት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አፈ-ጉባኤው ገልጸው፤ ለነዚህ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት በትብብር ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል፡፡
የፓን አፍሪካ ፓርላማ ተጠባባቂ ፕሬዘዳንት ዶክተር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው በአፍሪካ እየተባባሰ የመጣው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባላትና ቋሚ ኮሚቴዎች እያካሄዱት ያለው የጋራ ስብሰባ ለአራት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያካሂድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡