ባለፈው ሳምንት 3ኛው የኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ስብሰባ ሲጀመር አኅጉሪቱ ለገጠሟት ችግሮች መፍትኄ ለመፈለግ የአፍሪቃ አገራት ምን አይነት ሚና ሊኖራቸው ይችላል? በሚለው ጉዳይ ላይ አተኩሮ ነበር። በስብሰባው የተገኙት የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የአፍሪቃ መሪዎች ፖለቲካዊ፣ የፋይናንስ እና የግብር ማሻሻያዎች ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው ሲሉ ተናግረዋል። ሜርክል እንዳሉት የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ መዋዕለ-ንዋይ ለመሳተፍ ፈቃደኞች ናቸው። ነገር ግን መሠረታዊ ለውጦች ያስፈልጋሉ።
አንጌላ ሜርክል «እኛ ከፍ ያለ ግልፅነት በእነዚህ አገሮች ባለወረቶችን ያበረታታል ብለን እናምናለን። ምክንያቱን እንደ ጀርመን መካከለኛ ኩባንያዎች ያሉ የቡድን 20 አገራት ባለወረቶች በሥራቸው የሚመኩበት እምነት እና ግልፅነት ዋንኛ ጉዳይ ነው። በዚህም ሰዎች የት እና በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደምሰራ ያውቃሉ» ብለዋል።
እስካሁን 12 አገራት ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ በተባለው በአፍሪካ የግል መዋዕለ-ንዋይን የማበረታቻ መርሐ-ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል። ከእነዚህ መካከል ኢትዮጵያ፣ ርዋንዳ፣ ቤኒን፣ ኮትዲቯር፣ ግብፅ እና ጋና ይገኙበታል። በዘንድሮው ሶስተኛ ስብሰባ ከአፍሪካ የተሳተፉ መሪዎች ቁጥር ከቀደሙት ያነሰ መሆኑ ምን አልባት የአኅጉሪቱ ፖለቲከኞች በመርሐ-ግብሩ ያሳደሩት ተስፋ ተሟጦ ይሆን? የሚል ጥያቄ ያጭራል። በበርሊኑ ጉባኤ የተገኙት ከመርሐ-ግብሩ ዐሥራ ሁለት አባል አገራት የሰባቱ መሪዎች ብቻ ናቸው። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የደቡብ አፍሪቃው ሲሪል ራማፎሳ አልነበሩም።
መራሔተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በአፍሪካ የግል መዋዕለ-ንዋይን ለማበረታታት መንግሥታቸው የተለያዩ መርሐ-ግብሮች መንደፉን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት እንኳ የጀርመን እና የአፍሪካ ኩባንያዎች የሥራ ዕቅዶችን ለመደገፍ የጀርመን መንግሥት የአንድ ቢሊዮን ዩሮ ድጋፍ ይፋ አድርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ የጀርመን የልማት ሚኒስቴር «የማሻሻያ አጋርነት» የተባለ ስምምነት ከጋና፣ ቱኒዝያ እና አይቮሪኮስት ጋር ጀምሯል። ሌሎች አገሮች ይኸንንው ጥምረት ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዘንድሮው ጉባኤ ጎን ለጎን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቱኒዝያ የውሐ አቅርቦትን እንዲሁም በጋና የጨርቃ ጨርቅ እና የቸኮሌት ማምረቻ ፋብሪካዎች ግንባታዎችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች ለማድረግ ስምምነቶች ተፈራርሟል። ሜርክል እንዳሉት መንግሥታቸው የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪካ ገበያ እንዲሰማሩ ቢያበረታታም በመጨረሻ ግን ውሳኔው የኩባንያዎቹ ነው።
«በአፍሪካ መዋዕለ-ንዋይ የማፍሰሱ ውሳኔ የግሉ ዘርፍ ነው። ያንን ከማንም ሥራ ፈጣሪ ልንወስድ አንችልም። ልንረዳ፣ መተማመንን ልንገነባ፣ የኮምፓክት አባል በሆኑ አገሮች ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ ግልፅነት እንዳለ ልንናገር እንችላለች» ብለዋል።
ሜርክል በጉባኤው በሳህል ቃጠና ያለውን ሽብርተኝነት እና የአኅጉሪቱ የሕዝብ ቁጥር የሚያድግበትን ፍጥነት ጠቅሰው አፍሪካ ገና በርካታ ፈተናዎች እንዳሉባት አስጠንቅቀዋል። እንደ መራኂተ-መንግሥቷ ከሆነ ስደት እና የከባቢ አየር ለውጥን የመሳሰሉ አውሮፓ እና አፍሪካ የሚጋሯቸው ፈተናዎች ጭምር አሉ።
የአፍሪካ ኅብረትን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩት የግብፁ አብዱል ፋታኅ-ሲሲ በበኩላቸው የግል መዋዕለ-ንዋይ አፍሪካን በማረጋጋት እና ብልፅግናን በመፍጠር ኹነኛ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ተናግረዋል። ምዕራባውያኑ አገሮች ከአፍሪካ በሚኖራቸው ጠንካራ የንግድ ግንኙነት ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው «ጠንካራ አቅም፤ ጠንካራ ፖለቲካዊ ፍላጎት እና ግልፅ ርዕይ አለን። መዋዕለ-ንዋይ የአፍሪካን ገበያ ለማጠናከር ትልቅ ሚና ይጫወታል። ባለፈው ዓመት አፍሪካ በልማት እና በንግድ ረገድ ከጠንካራዎቹ አንዷ መሆኗን አሳይተናል» ብለዋል።
ለተቺዎች ግን ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ ተጨባጭ ለውጥ አላመጣም። መንግሥታት ስለ ውጥኑ ይፋ የሚያደርጓቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአስራ ሁለቱ አባል አገራት በዚሁ መርሐ-ግብር ተግባራዊ የሆነው መዋዕለ-ንዋይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የጀርመን ኩባንያዎች ያላቸው ፍላጎትም አነስተኛ ነው። በአፍሪካ የጀርመን መዋዕለ-ንዋይ ዕድገት ቢያሳይም በአሁኑ ወቅት በአኅጉሪቱ የተሰማሩ ኩባንያዎች ቁጥር 600 ገደማ ብቻ ነው። ከሰሐራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገራት የጀርመን ኩባንያዎች ማኅበር ሊቀ-መንበር ሐይንዝ ቫልተር ግሮሰ በእርግጥም የጀርመናውያኑ ፍላጎት ዘገምተኛ እንደሆነ በጉባኤው ተናግረዋል።
“ከአፍሪካ ወዳጆቻችን ከጀርመን የንግድ ማኅበረሰብ ከዚህ በላይ እንፈልጋለን የሚል ሐሳብ በተደጋጋሚ እሰማለሁ። ቃላችንን ወደ ተግባር እንቀይራለን» ያሉት ሐይንዝ ቫልተር ግሮሰ ለጉባኤው ተሳታፊዎች «ፍጥነቱን መጨመር አለብን» ብለዋል። በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰለሞንም ቢሆኑ አፍሪካ በይሁንታ ከተቀበለችው የጀርመን መዋዕለ-ንዋይ ከዚህ የበለጠ እንደምትጠብቅ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
አምባሳደር ሙሉ «ሒደቱ ጥሩ ነው። ነገር ግን አውሮፓውያን ወደ አፍሪካ መጥተው በፍጥነት በመዋዕለ-ንዋይ እንዲሳተፉ እንፈልጋለን። በእነዚህ ሁለት አመታት ወደ አፍሪካ ያመሩ ኩባንያዎች ቢኖሩም በቂ አይደሉም። ችግሮቹ ምክንያታዊ እንደሆኑ ብናውቅም ከፍላጎት፣ ቁርጠኝነት እና ሌሎች ዝግጅቶች አንፃር በቂ አይደለም እንላለን» ሲሉ አስረድተዋል።
የጀርመን ባለወረቶች አሁንም በአፍሪካ ገበያ ለመሳተፍ ቸልተኞች ናቸው። በተለይ የጀርመን ምጣኔ-ሐብት የጀርባ አጥንት እንደሆኑ የሚነገርላቸው አነስተኛ እና መካከለኛ ኩባንያዎች በአፍሪካ ገበያ የሚጀምሩት መዋዕለ-ንዋይ ኪሳራ ከገጠመው ኅልውናቸው አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ይሰጋሉ።
እንደ ፌራየን አፍሪካ ያሉ እና በአፍሪካ ገበያ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ጥብቅና የቆሙ ተቋማት የጀርመን መንግሥት በአፍሪካ የሚሰሩ ኩባንያዎች ደህንነት ለማስጠበቅ በመንግሥታቱ ላይ ጫና እንዲያሳድር ይወተውታሉ።
የዛኑ ያክል አምባገነን እየተባሉ የሚወቀሱ መንግሥታት ያሏቸው ግብፅ እና ርዋንዳን የመሳሰሉ አገሮች በመርሐ-ግብሩ መካተታቸው ከሲቪክ ማኅበራት ወቀሳ ቀስቅሷል። መርሐ-ግብሩ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለመዋዕለ-ንዋይ የሚሆኑ ደረጃዎች አላዘጋጀም የሚሉ ባለሞያዎች በበኩላቸው ለድህነት ቅነሳ ይኸ ነው የሚባል አስተዋጽዖ ለማበርከቱ እርግጠኞች አይደሉም። ይኸን ትችት ከሚጋሩት መካከል መቀመጫውን በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያደረገው እና ፖል የተባለው የጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ኔኔ ሞሪሾ አንዱ ናቸው።
ኔኔ ሞሪሾ “አብዛኛው ሕዝብ ምግብ፣ ውኃ፤ እና የጤና አገልግሎት በማያገኝበት ማኅበረሰብ ውስጥ የተጀመረ መዋዕለ-ንዋይ ትርፍ ብቻ መጠበቅ የለበትም። ማኅበራዊውን ነባራዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት አለበት። በኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ ውስጥ ያጣሁት ይኸንን ነው» ብለዋል።
እንደ ሮብ ፍሎይድ ያሉ እና በኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ የሚሳተፉ ግን አኅጉሪቱ ይኸ ዕድል ሊያመልጣት አይገባም የሚል አቋም አላቸው። መቀመጫውን በጋና ዋና ከተማ አክራ ያደረገው የአፍሪካ የኤኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ሮብ ፍሎይድ «በትክክል ከዚህ በላይ ሊደረግ የሚገባው ነገር አለ። የኮምፓክት አባል አገራት የየራሳቸውን ዕቅዶች ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊያስተዋውቁ ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ የቡድን 20 አገራት ኩባንያዎቻቸው በአፍሪካ ገበያ እንዲሰሩ ንቁ የመዋዕለ-ንዋይ ማስተዋወቂያ ማድረግ አለባቸው» ሲሉ ወደፊት መደረግ አለበት ያሉትን ጠቁመዋል።
ዳንኤል ፔልስ/እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አውሮጳ/ጀርመን