*…. አራቱም ክለቦች እንደሚሳተፉ አረጋግጠዋል….
*….ለከተማው እግርኳስ የሚዲያው ሚና የማይተካ ነው…..
የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው አመታዊ ውድድር በሰባት የውድድር አይነት ከህዳር 22/2016 ጀምሮ በደማቅ ሁኔታ እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል።
የፌዴሬሽኑ አመራሮች ዛሬ በከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መሰብሰቢያ አዳራሽ በሰጡት መግለጫ “በዘንድሮ የከተማው እግርኳሳዊ ውድድር ክለቦች ራሳቸውን ችለው ጠንክረው መጥተው የሚጫወቱበት ከብዛት ጥራት ላይ የምናተኩርበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ፌዴሬሽኑ አምና በነበረውና 134 ክለቦች በተሳተፉበት ውድድር ለሁሉም ክለቦች ከ48-68 ሺህ ብር መደጎሙን አመራሮቹ ገልጸው ከ2016 ጀምሮ ግን ከብዛት ወደ ጥራት እንደሚገባና አስፈላጊውን ክፍያ ክለቦቹ እንዲከፍሉ መወሰኑን አስረድተዋል። ፕሬዝዳንቱ አቶ ደረጄ አረጋ እንደተናገሩት “ክለቦችን በሁሉም ዘርፍ ማብቃት ይጠበቃል እስካሁን ተደጉመው ነው የመጡት መደጎሙም ልክ ነው እንደ ፌዴሬሽን ከማንኛውም አካል 10 ብር ተደጉመን አናውቅም የእኛና ከቅርብ ባለሀብት ወዳጆቻችን ገንዘብ ጠይቀን እንጂ በዜሮ
በጀት ነው የተንቀሳቀስነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“የከተማችን ክለብ ሆኖ አንድም ክለብ ወደ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ውድድር ማለፍ አልቻለም ዋናው ደግሞ የፋይናንስ ችግር ነው በቀጣይ አመታት ለማለፍ በሁሉም አቅጣጫ መስራት አለባቸው ኳሱ ቢያድግ ጥቅሙ ለሁላችንም ነው በሰለጠነው አለም እግርኳስ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን የቱሪዝም ምንጭ ነው ክለቦቻችንን ከፋይናንስ ድጎማ ውጪ ራሳቸውን እንዲችሉ በማገዝ ከጎናቸው ሆነን እጅ ለእጅ ተያይዘን መጓዝ ይጠበቅብናል” በማለት የፌዴሬሽኑን አቋም ገልጸዋል።
የመመዝገቢያ ገንዘብ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል ክለቦችም ቅሬታ እያቀረቡ ነው የተባሉት አመራሮቹ “ትልልቆቹን ክለቦች ጨምሮ ለሁሉም ክለቦች ከ48-68 ሺህ ብር ደጉመን እንደሻማ ቀልጠን ውድድሩን መርተናል አሁን ግን አይቀጥልም ለመመዝገቢያ 15 ሺህ ብር ብቻ ከፍለው ተወዳድረዋል ይሄ በየትኛውም የአገሪቱ ውድድር ላይ አልተደረገም አሁንም ያደረግነው ጭማሪ 75 በመቶ ብቻ ነው 25 በመቶ ደጉመናል ጭማሪ ከመደረጉ በፊት ታች ወርደን ጥናት አድርገናል አንድ ክለብ አንድ ማሰልጠኛ ስንት አገኘ..? ባለን መረጃ የጠየቅነው ብር ከሚያገኙት 20 እና 30 በመቶ አይበልጥም…ጭማሬው
የማይቀር ነው….. አንጫወትም አንሳተፍም ማለት አያስኬድም ውይይት እንጂ በማመጽ ማንም አያሸንፍም” ሲሉ ጠንካራ ምላሽ ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል ሳይጠናቀቅ ላልታወቀ ጊዜ ተራዝሞ የነበረው የአዲሰ አበባ ከተማ ዋንጫ ኢትዮጵያ ቡና ከሀድያ ሆሳዕና ጋር በሚያደርጉት የፍጻሜ ጨዋታ ከነገ በስቲያ ረቡዕ 9 ሰዓት ይፈጸማል።
ፌዴሬሽኑ እንደገለጸው ረቡዕ 9 ሰዓት ከሚደረገው የፍጻሜ ጨዋታ በፊት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ መድንም የደረጃ ጨዋታ እንደሚካሄድ ተገልጿል። ፕሬዝዳንቱ አቶ ደረጃ አረጋ እንደገለጹት “አራቱም ክለቦቻችን ከመቋረጡ በላይ ያሳሰባቸው ሌሎች ጉዳዮች ናቸው ከነሱ ጋር በጋራ ተነጋግረን ተስማምተናል ለዚህም ሁሉንም ክለቦች አመሰግናለሁ” ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ “የአዲስ አበባ እግርኳስ እንዲያድግ በክለቦችና በፌዴሬሽኑ ጥረት ብቻ የሚሆን አይደለም ሚዲያው ተገቢውን ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ተየናገሩ።
“እኔ ወደ ፌዴሬሽኑ ስመጣ ፌዴሬሽኑ በሩ ዝግ ነው ይባል ነበር ዘንድሮ ግን በራችንን በደንብ ከፍተናል ብለን እናምናለን ከአሉባልታ ይልቅ በመረጃና ማስረጃ ያለውን ሂደት መርምሮ ለህዝብ የምታሳውቁ እንድትሆኑ በእኛ በኩል ያለውን በር ከፍተናል ሚዲያው ከጎናችን እንዲሆን እጠይቃለሁ” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ አቶ ደረጄ ተናግረዋል።
“የከተማው እግርኳስ እንዲያድግ የመገናኛ ብዙሃኑ ሚና የማይተካ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ፌዴሬሽናቸው በሩን ክፍት አድርጎ ለእግርኳሱ ዕድገት በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።