ካለፈው አርብ ጀምሮ የዓለም መሪዎች በአውሮፓና ብርታኒያ ለጉባኤ ተቀመጠዋል። ባለፈው ቅዳሜና እሁድ የቡድን ሀያ አገሮች የመሪዎች ጉባኤ በሮም፤ ክትናንት ጀምሮ ደግሞ ለአየር ለውጥ ጉባኤ በብርታኒያ ግላስኮ ከተማ። የዓለምን ኢኮኖሚ 80 ከመቶ ይይዛሉ የሚባሉት የቡድን ሀያ አገሮች መሪዎች በሮሙ ጉባኤያቸው ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ በአየር ለውጥ፣ የኩባንያዎች ታክስ፣የኮቪድ ክትባት ስርጭትን በሚመለከትና ለታዳጊ አገሮች ሊሰጥ ስለሚገባው የልማት እርድታ ከስምምነት የደረሱ መሆኑ ተገልጿል።
በተለይ በአየር ለውጥ ላይ ያስተላለፉት ውሳኔና የደረሱበት ስምምነት ባለፈው እሁድ ተጀምሮ ለሁለት ሳምንታት በሚቆየው የአየር ለወጥ ጉባኤ ስኬት ትልቅ ግባት ሊሆን እንደሚችል ነው የሚገመተው። ወደ ከባቢ አየር የሚገባውን የካርቦን ልቀት መጠን ለመቀነስና የአለማችንን የሙቀት መጠን ወደ 1.5 ዲግሪ ሲሊሺየስ ዝቅ ለማድረግ፣ ከሰልን ለመሳሰሉት በካይ የሀይል ምንጮች የሚደረግን ማናቸውንም መዋዕለ ነዋይ ለማቆም፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ፍይናንስ 100 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ የተገባውን ቃል እውን ለማድረግ የተስማሙ ስለመሆኑም በመግለጫው ተዘርዝሯል።
ኮቪድን ለመከላከልና ክትባቱን ለማሰራጨትም የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ 40 ከመቶ፤ እስከሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ደግሞ 70 ከመቶ የሚሆነውን የዓለም ህዝብ ለመክተብ የያዘውን እቅድ ለማሳከት እንደሚሰሩና ለድሀ አገሮች እንደሚረዱ ቃል ገብተዋል።
መሪዎቹ በአየር ንብርት ለውጥ ላይ ያሳለፉት ውስኔ ለግላስጎው ጉባኤ ግብና ስኬት የሚያግዝ ነው ቢባልም፤ ለአየር ንብረት ለወጥ ተክራካርዎች ግን ውሳኔው ያነሰና ከተጠበቀው በታች ነው።በኮቪድ ወረርሺኝ ክትባት ስርጭት በኩልም መሪዎች ሲገናኙ የሚገቡት ቃልና ተግብራቸው የማይገናኝ እየሆነ መቸገራቸውን የቀድሞው የብርታኒያ ጠቅላይ ሚኒስተርና በአሁኑ ወቅት የአለም የጤና ድርጅት አምባሳደር ሚስተር ጎርደን ብራውን ሲናገሩ ተሰምተዋል፤ «ቦሪስ ጆንሰን በቡድን 7 የመሪዎች ጉባኤ ላይ አለምን እከትባለሁ ብለው ነበር።
ከዚያ ወዲህ የተደርገው ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደልም` በማለት በመሪዎች ዘንድ የቃልና ተግባር አንድነት ችግር ያለ መሆኑን ገልጸዋል። ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን ውይይት ከተደረገባቸው አጀንዳዎች መካከል የፈርንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኖኤል ማክሮንና የአሜርካው ጆባይደን ከሳምንታት በፊት አሜሪካ ከብርታኒያና አውስትራሊያ ጋር ፈረንሳይን በማግለል የፈረመችው ወታደራዊ ስምምነት ይገኝበታል።
የአውሮፓ ኮሚሺን ፕሬዝድንት ኡርሱል ቮንዴር ሌየንና ፕሬዝድንት ባይደን በነበራቸው የጎን የሁለትዮሽ ስብሰባም ፕሬዝድንት ትሩምፕ በብረትና አሉምኒየም ላይ ጥለውት የንበረውን ታሪፍ ፕሬዝዳንቱ ለማንሳት በመስማማት በሁለቱ ወገኖች የንግድ ግንኑነት ላይ ከተደቀኑት ችግሮች አንደኛውን አቃለዋል ተብሏል። ፕሬዝዳንት ማክሮን ከጠቅላይ ሚኒስተር ጆንሰን ጋርም እንደዚሁ በጎንዮሽ ተገናኝተው በሁለቱ መካከል ስለተፈጠረው የአሳ ማጥመጃ ክልል ውዝግብ ተወያይተዋል።
ብርታኒያ ከአውሮፓ ህብረት ከወጣች በኋላ በህብረቱና ብርታኒያ መካከል በተደረሰው የንግድ ስምምነት ላይ አስቸጋሪ ከነበሩት ዘርፎች አንዱ የአሳ አጥማጆች መብትና ግዴታ ጉዳይ ነበር። ከብዙ ውዝግብና ድርድር በኋላ የተደርሰው ስምምነት፤ የአውሮፓ ህብረት የአሳ ጀልባዎች እስከሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ድረስ በብራታኒያ የውሀ ክልልም እንዲሰሩ ቢፈቅድም፤ የብርታኒያ ጀልባዎች ግን የበለጠውን ዕድል እንዲያገኙ ይጠይቃል።
ከ2021 እስከ 2026 ባለው ግዜ ውስጥም ቀስ በቀስ የብርታኒያው የውሀ ክልል ለብርታንያ ጀልባዎች የሚተላለፍ ሆኖ፤ በ2026 ብርታኒያ የህብረቱን ጀልባዎች ወደ ውሀዋ እንዳይገቡ ልትከለክል ትችላለችም ይላል። ይህ ሲሆን ግን ህብረቱ ወደ አውሮፓ በሚገባው የብርታኒያ የአሳ ምርት ላይ ታክስ ሊጨምር ወይንም የብርይታኒያ የአሳ ጀልባዎች ወደ ህብረቱ ውሀ ጭራሽ እንዳይደርሱ ሊያደርግ ይችላል።
በአሁኑ ወቅት የስምምነቱ የመጅመሪያው ደረጃ ላይ ቢኮንም፤ ፈረንሳይ ግን የተወሰኑ ጀልባዎች ፈቃድ ተክልክለዋል በማለት ተቃውሞ ስታሰማ ቆይታ፤ ባለፈው ሳምንት የብርታኒያን ጀልባ በማሰር ጭምር ተቃውሙዋን ገልጻለች። ሁለተ መቶ የሚሆኑ የፈረንሳይ ጀልባዎች ፈቃድ የተሰጣቸው ቢሆንም ከዚያም በላይና የዚህን እጥፍ ለሚሆኑ ጀልባዎች ሊሰጥ ይገባል ነው የፈረንስይ ባለስልጣናት ጥያቄ። ይህ ካልሆነም የብርታኒያን ጀልባዎች በፈረንሳይ ባህር እንዳይጠቀሙ ብቻ ሳይሆን ሌሎች እርምጃዎችን ለምሳሌ በጭነት መኪናዎች ላይ ቁጥጥር የማድረግ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። የፈረንስይ የአውሮፓ ጉዳይ ሚኒስተር ሚስተር ክሌሜንት ቢውክ የብርታኒያ ድርጊት ተገቢ ያልሆነና ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ተገደናል፤ የብርታኒያ መንግስት የሚገባውም እንደዚህ አይነት እርምጃ ነው ሲሉ ተሰምተዋል።
ተፎካካሪም ተቀናቃኝም እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፈረንሳይና ብርታኒያ አለመተማመንም እንደሚታይባቸው ነው በዲፕሎማቶች ዘንድ የሚነገረው ። በቅርቡ ብርታኒያ ከእሜሪካና አውስትራሊያ ጋር የገባችበት ወታደርዊ ስምምነት፤ ፈረንሳይን ካውስትራሊያ ጋር የነበራትን በቢሊዮን የሚቆጠር ኢሮ ግብይት አስቀርቶባታል።ፕሬዝዳንት ማክሮን በቅርቡ በፋይናንሺያል ታይምስ ላይ በሰጡት አስተአያየት `ለአመታት ተደራድረህ የተስማማህበትን ትንሽ ቆይተህ ከስምምነቱ ውጭ የምትፈጽም ከሆነ፤ ተአማኒነተህን ጥርጥሬ ውስጥ ይከተዋል` ማለታቸው የሁለቱን አገሮች ብሎም በብርታኒያና የአውሮፓ ህብረት መካከል በቀጣይም ሊኖር የሚችለውን አለመግባባትና ውዝግብ የሚጠቁም ነው።
ብርታኒያ ግን የፈርነሳይን ወቀሳ አትቀበልም። በውሀዋ እንዲሰሩ ለጠየቁ ጀልባዎች ከብሬክዚት በፊት በዚህ ውሀ ላይ ይሰሩ የነበር መሆኑን እያረጋገጥን ፈቃድ ሰተናል በማለት ነው ባለስልጣኖቿ የሚከራከሩት። የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ሚስ ሊዝ ትሩስ፤ ፈረንሳይ በአሳ እንዱስትሪያቸው ላይ እየወሰደችው ያለው እርምጃና የምትስነዝረው ማስፈራሪያ ተቀባይነት የለውም በማለት በ 48 ሰአት ውስጥ ይህን ሕገወጥ እርምጃ ካልቀለበሰች ብርታኒያ የበኩሏን ህጋዊና አጸፋዌ እርምጃ ትወስዳለች በማለት ትናንት ለመገናኛ ብዙሀን ተናገረዋል።፡ ፈረንሳይ እየስራች ያለችው ልክ አይደለም። በንግድ ስምምነቱ መሰረት አንድ አጋር ስምምነቱን ካፈረሰ ወይም ከስምምነቱ ውጭ ከሰራ፤ ሕግዊ ርምጃ ሊወስድበትና ካሳም ሊጠየቅ ይገባል፤` በማለት ብርታኒያም የምታደርገው ይህንኑ መሆኑን አስታውቀዋል። ሆኖም አሁን ሁለቱም መንግስታት ያስቀመጡትን ቀነ ገደብ እንድራዘሙት ተሰምቷል።
ያአሳ ህብትና ግብይት ለሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚ ያለው ተዋጾ አነስተኛ እንደህነ ነው የሚነገረው፣ ከጠቅላላ ምርታቸው ጂዲፕ ከ0.1 ከመቶ አይበልጥም። በዚህም ምክኒያት የውዝግቡ መነሻ ከኢኮኖሚው ይልቅ ፖለቲካ እንደሆነ ነው ብዙዎች የሚያምኑት። ውዝግቡ የተካረረውና ከዚህ ድረጃ የደርሰው ፕሬዝዳንት ማክሮን በመጭው ሚያዚያ ምርጫ ስላለባቸውና ጠቅላይ ሚኒስተር ቦሪስ ጆንሰንም የብሬክዚት ድጋፊዎችን ስሜት ለመግዛት ነው የሚሉ ድምጾች ይሰማሉ። ውዝግብ ክርክሩ በሁለቱ አገሮች ካልተፈታና ወደ ህብረቱ ከመጣ፤ ከብሬክዚት በኋላ የተከፈተ የመጅመሪያው የህብረቱና የብርታኒያ የንግድ ክርክር ነው የሚሆነው።በቅርቡም የብሬክዚት ውል በስሜን አየርላንድ ላይ ባስቀመጠው ድንጋጌና ትርጉም እንደዚሁ ያልተቁጨ ውዝግብ መነሳቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ብርታኒያ ያሁኑ ከፈረንሳይ ጋር የገባችበት ውዝግብም ከእንግዲህ የብርታኒያ ህይወት ከጎረቤቶቿና የአውሮፓ ህብረት ጋር በሚፈጠሩ ውዝግቦችና አለመግባባቶች የታጠረ እንደሚሆን የሚያመላክት ነው ይላሉ፤ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ታዛቢዎች።
ገበያው ንጉሤ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አውሮጳ/ጀርመን