አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከ60 ዓመት በኋላ አፍሪካውያን በአንድነት ተሰባስበው በአመራር የሚበቁበት አካዳሚ በስጦታ ይዛ መምጣቷን የአፍሪካ አመራር ልሕቀት አካዳሚ አስታወቀ። የፓን አፍሪካኒዝምን መንፈስ እንደገና በማነቃቃት አፍሪካ ለሚገጥሟት ችግሮች መፍትሔ መስጠት እንዳለባትም ተጠቁሟል።
የአፍሪካ አመራር ልሕቀት አካዳሚ ርዕሰ አካዳሚ ዶክተር ምሕረት ደበበ ትናንት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ በ36ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከሚካሄዱ ፎረሞች መካከል ‹‹ፓን አፍሪካኒዝምን እንደገና ማደስ›› በሚል መሪ ቃል አፍሪካዊነትን ጠቅልሎ በሚይዝ ጽንስ ሀሳብ መሠረት የፓን አፍሪካኒዝም ፎረም የካቲት 12 በአፍሪካ አመራር ልሕቀት አካዳሚ ይካሄዳል።
እንደ ዶክተር ምሕረት ማብራሪያ፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሠረተበትን 60ኛ ዓመት ጊዜ ላይ በመሆናችንና አጀንዳ 2063 የልማት ግብ አስረኛ ዓመቱ የሚከበርበት በመሆኑ 60 ዓመት የሆነውን የፓን አፍሪካኒዝምን መንፈስ ወይም የፓን አፍሪካኒዝም እይታን እንደገና ለማነቃቃት ፎረሙ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መጀመሪያ ሲመሠረት ኢትዮጵያ ዋና ጽሕፈት ቤቱን ሰጥታ ሀሳቡን ከጠነሰሱ ጥቂት ሀገሮች መካከል ሆና የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ በሰፊው ማስጀመሯን ጠቅሰዋል።
አፍሪካውያንን አነሳስቶ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመዋጋት አፍሪካውያን ለመጨረሻ ጊዜ ነጻ ለመሆን የፓን አፍሪካኒዝምን እንቅስቃሴ አድርገው ነበር ያሉት ዶክተር ምህረት፤ ነጻ የመሆን ዓላማው ከተሳካ በኋላ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እየሳሳ መጥቷል ብለዋል።
ነገር ግን አሁንም አፍሪካ ችግር ውስጥ በመሆኗ የፓን አፍሪካኒዝምን እንቅስቃሴ መጠቀም አስፈላጊ ነው ያሉት ዶክተር ምህረት፤ በአጠቃላይ የአሁን ዘመን አፍሪካውያን የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብን እንደገና አንስተው አፍሪካ ለገጠሟት ችግሮች ምላሽ እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የዓለማችን ኃያላን ሀገራት ፊታቸውን ወደ አፍሪካ የመለሱበት ጊዜ ነው ያሉት ዶክተር ምሕረት፤ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ዳግም እንዳይመጣ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል አፍሪካውያን በከፍተኛ ንቃት የአፍሪካ ዳግም ህዳሴ እንዲፈጠር የተለያዩ መነሳሳቶች አሉ። አፍሪካ ታድሳ ታላቅ አህጉር ትሆናለች? ወይንስ አፍሪካ እንደ ገና በቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ትወድቃለች? የሚለው ጥያቄ የሚመልሱት አፍሪካውያን ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል አፍሪካውያን በአንድነት ተሰባስበው በአመራር የሚበቁበት አካዳሚ ከ60 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ አዲስ ስጦታ ይዛ መጥታለች ሲሉም አክለዋል።
እንደ ዶክተር ምሕረት ማብራሪያ፤ ይህ ታሪካዊ ወቅት የአፍሪካ አመራር ልሕቀት አካዳሚን ለአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት የምናስተዋውቅበት ጊዜ ነው። አካዳሚው ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ አመራሮችን ሲያሰለጥን ቆይቷል። በመንግሥት አመራሮች ብቻ ያተኮረ ሳይሆን የግል ዘርፉን፣ የሲቪል ማኅበራትንና የሕዝብ አገልግሎት ላይ ያሉ መሪዎችን ሁሉ የሚያሰለጥን ነው። እንዲሁም ልዩ ልዩ ጥናቶችን በማድረግ የፖሊሲ ምክርን ለመሪዎች የሚያቀርብ አካዳሚ ነው ብለዋል።
እንደ ርዕሰ አካዳሚው ገለጻ፤ ፎረሙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ አምባሳደሮች፣ ከፍተኛ ምሑራንና ጽሑፍ አቅራቢዎች ይገኛሉ። በአፍሪካ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ምሑራን ጥናታዊ ጽሑፎችን ያቀርባሉ። መሪዎችም ሀሳባቸውን ያካፍላሉ። ፓን አፍሪካኒዝምን ለማጠናከር የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ ይቀርባል። አፍሪካ ደሃ እንዳልሆነችና ጠንካራ መሪዎችና ልጆች ማፍራት እንደምትችል ኢትዮጵያ ሀሳብ ታካፍላለች።
ከዚህ በኋላም በየዓመቱ ከሚጠበቁ ፎረሞች መካከል አንዱ የአፍሪካ አመራር ልሕቀት አካዳሚ የፓን አፍሪካኒዝም ፎረም ይሆናል ሲሉ ዶክተር ምሕረት ተናግረዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም