ብሪታኒያ ባለፈው ሚያዚያ ወር በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር ቦሪስ ጆንሰን አማካይነት ስደተኖችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ የሚያስችል የ126 ሚሊዮን ዩሮ ስምምነት ብታደርግም ተግባራዊነቱ ግን በአውሮጳ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነት ታግዶ ቆይቶ ነበር። በርካታ የስደተኞችና የመብት ተከራካሪ ድርጅቶችም ስምምነቱን መቃወም ብቻ ሳይሆን፤ በብሪታኒያ መንግሥት ላይ ስደተኞችን ወደሌላ ሦስተኛ አገር በመላክና የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕጎችንና የስደተኞችን መብት ድንጋጌዎችን በመጣስ ክስ አቅርበው ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ ነው፤ ሰኞ ዕለት የለንደኑ ፍርድ ቤት መንግሥትን የሚደግፍ ብይን የሰጠው። የፍርድ ቤቱ ዋና ዳኛ ሚስተር ክሊቨ ሌዊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ፤ መንግሥት ከሩዋንዳ ጋር ስምምነት በማድረግ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ሊልክና የጥገኝነት ጥያቄያቸውም ከብሪታኒያ ይልቅ በሩዋንዳ በኩል እንዲወሰን ሊያደርግ የሚችል መሆኑን በመግለጽ፤ አፈጻጸሙ ክብሪታኒያም ሆነ ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር አይጻረርም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተር ሪሺ ሱናክ በበኩላቸው «የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በደስታ ነው የተቀበልኩት። ምክንያቱም አሠራሩ በሕገወጥ መንገድ ወደ ብሪታኒያ የሚገቡት ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ ሊያገኙ እንደማይችሉና ይልቁንም ወደ አገራቸው ወይም ወደ ሌላ እንደ ሩዋንዳ ያለ አማራጭ አገር የሚላኩበትን አሠራር የሚፈጥር ነው» በማለት መንግሥታቸው ለተግብራዊነቱ ፈጥኖ እንደሚንቀሳቀስ አስታውቀዋል።
የመብት ተከራክሪዎች፤ የስደተኞችና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፤ የሕግ ባለሙያዎች ግን በውሳኔው ላይ ያላቸውን ተቃውሞ እየገለጹ ነው። የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተክትሎ ባወጣው መግለጫ « የብሪታኒያና ሩዋንዳ ስምምነት ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስና ስደተኞችን ከአንድ አገር ወደሌላ ለማስተላለፍ የተቀመጡ ሕጎችንና አሠራሮችን ያልተከተለ ነው» ሲል ተቃውሟል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ የሁለቱን አገሮች ስምምነትም ሆነ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሁሉም ሊቃወመው ይገባል ሲል ጥሪ አቅርቧል። በብሪታኒያ የአምንስቲ ኢንተርናሺናል የስደተኞችና ፈላስያን መብት ዳይሬክተር ሚስተር ስቴቨ ቫልዴዝ ስይሞንድስ ስምምነቱንም ሆነ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለመቃወም ከሚያስችሉ ምክንያቶች ውስጥ፤ «የሩዋንዳ የራሷ የሰብአዊ መብት ታሪክና ብሪታኒያ ወደ አገሯ የገቡትን ስደተኞች የጥገኘነት ጥያቄ እራሷ ልታስተናገድ ሲገባ ወደ ሩዋንዳ በማስተላለፍ ከኃላፊነት ለመሸሽ መሞከሯ» በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
የሕግ ባለሙያና የስደተኞች ጠበቃ ሶፊ ሉካስም፤ «በሩዋንዳ ያለው የስደተኞች የአቀባበል ሥርዓትና የፖለቲክ ነጻነቱ ጉዳይ አሳሳቢ ነው» በማለት ወደዚያች አገር ጥገኝነት ጠያቂዎችን መላክ በምንም መስፈርት ቢሆን ትክክል አይሆንም ነው ያሉት።
በብሪታኒያ የስደተኞች ምክር ቤት ኃላፊ ሚስተር ኤንቨር ሶሎሞን በበኩላቸው ጥገኘት ጠይቂዎችን ወደ ሌላ አገር ማስተላለፍ የጭካኔ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፤ «ብሪታኒያ ይህንን የምታደርግ ከሆነ በዴሞክራሲዋና ታሪኳ ትልቅ ጠባሳ ነው የሚሆነው» በማለት መናገራቸው ተዝግቧል።
ብሪታኒያ በአውሮጳ፤ ከፈረንሳይ፤ ጀርመንና ጣሊያን የበለጠ የስደተኞች ቁጥር ባይኖራትም የስደተኞች ጉዳይ ግን በሀገሪቱ ዋና የፖለቲካ አጀንዳ ነው። በሥልጣን ላይ ያለው የወግ አጥባቂዎች ፓርቲ ወደ ሥልጣን የመጣውም ሆነ አገሪቱን ከአውርጳ ኅብረት ያስወጣው በስደተኞች አጀንዳ ሲሆን፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒተር ቦሪስ ጆንሰን ከሩዋንዳ ጋር ስምምነቱን የፈጸሙትም ይህንኑ የስደተኞችን አጀንዳ ለማስፈጽም እንደነበር ነው የሚታመነው። ከዚይም ወዲህ ወደ ሥልጣን የመጡትና ያሁኑም ጠቅላይ ሚኒስተር ሪሺ ሱናክ በስደተኞች ላይ ጥብቅ እርምጃ በመውሰድ ለፓርቲያቸውና ለራሳቸው የህዝብን ድጋፍ ማስገኘት ዋና ፍላጎታቸው እንደሆነ ነው የሚነገረው።
ይሁን እንጂ የጠቅላይ ሚኒስተር ሱናክ መንግስት አሁኑኑ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ ስድተኖችን ወደ ሩዋንዳ እንደማይልክ ነው የሚታወቀው። ከተቃውሞውና ውግዘቱ በተጨማሪ፤ የመብት ተከርክሪ ድርጅቶችና የህግ ጠበቆች የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ይግባኝ በማለት ወደ ሌላ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱትና ከዚያም እስከ አውሮፓ ፍርድ ቤት ሊደርስ እንደሚችል፤ በዚህ ሁሉ ሂደትም የወራት ምናልባትም የአመታት ጊዜ ሊወስድ እደሚችል ነው የህግ ባሙያዎች የሚናገሩት።
ገበያው ንጉሤ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አፍሪቃ