ብሪታንያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ፣መሠረቱ የውጭ የሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰይማለች።እስያዊ ብሪታንያዊው የወግ አጥባቂው ፓርቲ ፖለቲከኛ ሪሺ ሱናክ ዛሬ 57ተኛው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።የብሪታንያ ንጉስ ቻርልስ ሳልሳዊ ሹመታቸውን ያጸደቁላቸው የቀድሞው የብሪታንያ የገንዘብ ሚኒስትር ሱናክ ዛሬ መንበረ ስልጣኑን ተረክበዋል። በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ በኋላም ጽህፈት ቤታቸው ፊት ለፊት ባደረጉት ንግግር መንግሥታቸው በዋነኛነት ሊያከናውን ያቀዳቸውን ሥራዎች ጠቁመዋል፤ቃልም ገብተዋል።
«ኤኮኖሚውን ማረጋጋትና መተማመንን ማስፈን፣ የመንግሥት ዋነኛው አጀንዳ እንዲሆን አደርጋለሁ። ይህም አስቸጋሪ ውሳኔዎች ይከተላሉ ማለት ነው። እኔ የምመራው መንግሥት፣ እኛ በጣም
ደካማ በመሆናችን መክፈል ያልቻልነውን እዳ ለቀጣዩ ትውልድ፣ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ ፣ አይተውላቸውም። ሀገራችንን አንድ አደርጋለሁ። በቃላት ሳይሆን በተግባር እንጂ።»
በብሪታንያ የስድስት ዓመት ታሪክ አምስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ፣የመጀመሪያው መሠረታቸው የውጭ የሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ከ200 ዓመታት በላይ የበብሪታንያ ታሪክ ወጣቱ መሪም ናቸው። የ42 ዓመቱ ሱናክ የሚተኩት፣ በተቃውሞና ግፊት ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ካሳወቁ በኋላ ዛሬ ለንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ አስገብተው የተሰናበቱትን የወግ አጥባቂ ፓርቲ ፖለቲከኛ ሊዝ ትራስን ነው። ትረስ ፣ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ከመሞታቸው ከሁለት ቀናት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየሙ በኋላ ስልጣን ላይ የቆዩት ለ44 ቀናት ብቻ ነበር። ብሪታንያን ለአጭር ጊዜ የመሩትን ትራስን የተኩት ሱናክ፣ ለፓርቲያቸው መሪነት ከተመረጡበት ጊዜ አንስቶ፣ በስልጣን ዘመናቸው ይጠብቋቸዋል የተባሉ ተግዳሮቶች የብዙዎችን ትኩረት
ስበዋል። ለሊዝ ውድቀት ምክንያት የሆኑት፣ ብሪታንያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገጠሟት የኤኮኖሚ ችግሮች ከፈተናዎቹ ዋነኛው ተብሏል። በወግ አጥባቂ ፓርቲያቸው ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል እና አለመረጋጋትም ሌላው ሱናክ የሚጠብቃቸው ፈተና ነው። ሱናክ ትናንት ለፓርቲያቸው መሪነት ከተመረጡ በኋላ ባሰሙት ንግግር እነዚህን ችግሮች መጋፈጣችን አይቀርም ብለዋል፤መፍትሄ ያሉትንም ጠቁመዋል።
«ብሪታንያ ታላቅ ሀገር ናት።ሆኖም በጣም ጠንካራ ኤኮኖሚያዊ ፈተና እንደገጠመን አያጠራጥርም።አሁን መረጋጋትና አንድነት ያስፈልገናል።ፓርቲያችንንና ሀገራችንን አንድ ማድረግ ቅድሚያ ትኩረት የምሰጠው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ይህ የተጋረጡብንን ፈተናዎች መወጫውና ፣ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን የተሻለች ይበልጥ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት ብቸኛው መንገድ ነው። »
ሱናክ ለችግሩ መፍትሄ ቢያቅድሙ ብሪታንያን አሁን የሚንጠው የኤኮኖሚ ችግር ትልቁ ፈተናቸው ሆኖ መዝለቁ እንደማይቀር ነው የሚነገረው ። የለንደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነህ እንደሚለው ግን
ኅብረተሰቡ በበኩሉ ካላቸው ልምድ በመነሳት ቀውሱን ያሻሻሉ ብሎ ይጠብቃል።
ከሰባት ዓመት በፊት የብሪታንያ ፓርላማ አባል የሆኑት ሱናክ ፣በአጭር ጊዜ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን መብቃታቸው አስገርሟል። ሱናክ ይበልጥ የታወቁት በቅርቡ ነው። ከዛሬ ሁለት ዓመት ወዲህ ። የለንደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነህ እንደሚለው በተለይ የገንዘብ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የወሰዷቸው እርምጃዎች ናቸው ይበልጥ ታዋቂ ያደረጓቸው።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል ጥብቅ ሕግ አውጥተው፣ራሳቸው ሕጉን መጣሳቸው ፖሊስ ማረጋገጡና በኋላም በስነ-ምግባር ጉድለት የሚጠረጠሩ ፖለቲከኛን በመሾም በፈጸሙት የስነ ምግባር ቅሌት ስልጣናቸውን ከአንድ ወር ከአሥራ ዘጠኝ ቀን በፊት ከለቀቁ በኋላ ወግ አጥባቂው ፓርቲ እርሳቸውን ለመተካት ሱናክንና ሊዝ ትረስን በእጩነት ሲያቀርብ ደግሞ እውቅናቸው ይበልጥ ጨመረ ።
ከብሪታንያ ባለጸጋ የፓርላማ አባላት አንዱ ሱናክ በጎርጎሮሳዎው 1960 ዎቹ ከምሥራቅ አፍሪቃ ወደ ብሪታንያ ከተሰደዱ ህንዳውያን ወላጆቻቸው በጎርጎሮሳዎው ግንቦት 1980 በሳውዝሀምፕተን ብሪታንያ ነው የተወለዱት። ከህንድዋ የፑንጃብ ግዛት ዝርያ ያላቸው ባታቸው ያሽቪር ሱናክ ኬንያ ተወልደው እዚያው ኬንያ በሐኪምነት አገልግለዋል ።ታንዛንያ የተወለዱት እናታቸው ኡሻ ሱናክ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ሳውሀምፕተን በሚገኘው «ሱናክ መድኃኒት ቤት» በተባለው የግል መድኃኒት ቤታቸው አስተዳዳሪና የፋርማሲ ባለሞያ ናቸው። ሪሺ ሱናክን ጨምሮ ሦስት ልጆች አሏቸው ። የቡክር ልጃቸው ሱናክ ከታዋቂው የብሪታንያው ኦክስፎርድ ሊንኮለን ኮሌጅ ፣በፊሎሶፊ፣በፖለቲካ እና በኤኮኖሚ ትምሕርቶች በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል። ከካሊፎርንያ ስታንፈርድ ዩኒቨርስቲም በንግድ አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። በዚሁ ዩኒቨርስቲ ነበር ሱናክ የህንዳዊውን ቢሊዮነር ነጋዴ ልጅ ፣ባለቤታቸውን የተዋወቁት።ባለቤታቸውና ሱናክ ከብሪታንያ ሀብታሞች 222ኛው ደረጃ የተሰጣቸው ባለጸጋዎች ናቸው። የሱናክ አያትም ታዋቂ ሰው ናቸው። የብሪታንያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ፖለቲከኛ ሪሺ ሱናክ ትናንት በፓርቲያቸው መሪነት እስከተመረጡበት ጊዜ ድረስ የብሪታንያ ዋነኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የብሪታንያን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት አጠቃላይ ምርጫ እንዲጠራ ጥሪ ሲያቀርቡ ነው የቆዩት።ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው የተረጋገጠላቸው ሱናክ ግን ይህን የሚቀበሉ አይመስልም።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ
አውሮጳ/ጀርመን