ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ የደረሰው ግጭት ያስከተላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሚመለከት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመጉ) መስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ ምላሽ የሰጠው የጋምቤላ ክልል ግን በከፍተኛ ተቃውሞ ነበር ሪፖርቱን እንደማይቀበለው ያስታወቀው፡፡
በተለምዶ ኦነግ ሸኔ እየተባለ የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) ታጣቂዎች በጋራ በመሆን፣ በጋምቤላ ከተማ ላይ ጥቃት ከፈቱ ይላል ኮሚሽኑ በሪፖርቱ፡፡ ከፌዴራልና ከክልል የፀጥታ ኃይሎች ጋር ውጊያ ከተደረገ በኋላ፣ ከተማዋን ወዲያው የመንግሥት ኃይሎች ተቆጣጠሩም ይላል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮም የፀጥታ ኃይሎች ለሁለት ተከታታይ ቀናት በከተማው ላይ በወሰዱት ዕርምጃ 50 ሲቪሎች ተገድለው 25 ቀላልና ከባድ የመቁልስ አደጋ ደርሶባቸዋል ሲል የምርመራውን ግኝት በሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡
ይህ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት ግን የክልሉን መንግሥት ሲያስቆጣ ነው የታየው፡፡ የጋምቤላ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጌቱ አዲንግ፣ ሪፖርቱን በጋምቤላ ክልል ያለውን ሁኔታ ያላገናዘበ ሲሉ ነበር የገለጹት፡፡ ‹‹ጋምቤላ ሁሉም በፍቅርና በሰላም የሚኖርበት ክልል ነው፤›› ያሉት አቶ ኡጌቱ፣ ግጭቱን ለመቆጣጠር የፀጥታ ኃይሎች ከባድ መስዋዕትነት ባይከፍሉ ኖሮ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሽብር ቡድኖቹ የከፋ ዕልቂት ያደርሱ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ውጊያው ከተማ ውስጥ የተደረገ እንደነበር ያመለከቱት አቶ ኡጌቱ፣ የሽብር ኃይሎቹ ከተማዋን ለመውረር አቅደው መንቀሳቀሳቸውን አስታውሰዋል፡፡ ከ50 በላይ ሲቪሎች ሞተዋል ተብሎ የቀረበውን የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት የተቃወሙት አቶ ኡጌቱ፣ ‹‹የፀጥታ ኃይሎች እንደ ጀግና መቆጠር ሲገባቸው እንደ ጨፍጫፊ መታየታቸው አግባብነት የለውም፤›› ብለዋል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርት ሁሉንም ወገን ሳያሳትፍ የተጠናቀረ መሆኑንም ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ ጁንታውንና የጁንታው ተላላኪ የሆኑ የኦነግ ሸኔና የጋነግ ድምፆችን ለይቶ የሚያስተጋባ የውሸት ሪፖርት ነው፤›› ሲሉ ሪፖርቱን የኮነኑት አቶ ኡጌቱ ፈጽሞ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል፡፡ የሪፖርቱን ዓላማም ‹‹ሆን ተብሎ ሕዝብ ከሕዝብ ለማጋጨት የተሠራ፤›› ሲሉ የገለጹት ኃላፊው፣ ሁሉንም መረጃና አካላት ሳያሳትፍ የተካሄደ ምርመራ መሆኑንም በዋናነት አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርብ ዓመታት በአንፃራዊነት ገለልተኝነቱን የጠበቀ የሥራ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ተብሎ ቢጠቀስም፣ በአንዳንድ ሪፖርቶቹ ግን ጠንካራ አፀፋ ሲገጥመው ይታያል፡፡ በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በጋራ አጥንቶ ያቀረበው ተቋሙ፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች በጦርነቱ የደረሱ ችግሮችንም ሪፖርት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህ ዓበይት ሪፖርቶች በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ የደረሱ የመብት ጥሰቶችን ጨምሮ፣ የሚቺሌ አባ ገዳ አባላትን ግድያ መርምሮ ሪፖርት አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የደረሰውን ድርቅ አስመልክቶ፣ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት ይፋ ማድረጉም አይዘነጋም፡፡
በእነዚህና በሌሎችም የሪፖርት ሥራዎቹ ጠንካራና በአንፃራዊነት ከተፅዕኖ ገለልተኛ የሚባል የሥራ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ስለመቆየቱ ሙገሳ ሲሰጠው ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በተቃራኒው ተቋሙ የሠራቸው ሥራዎችና ያቀረባቸው ሪፖርቶች አስከፍቶናል የሚሉ አካላት ተቋሙን ሲተቹት ቆይተዋል፡፡ ከፌዴራል መንግሥት ጀምሮ የክልል መንግሥታት የኢሰመኮ ተቃዋሚ ሲሆኑ የታየበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ ተቋሙ ገለልተኝነቱና ነፃነቱ የተጠበቀ ሆኖ መደራጀቱ ቢነገርም፣ የመንግሥት ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡ የተለያዩ ሪፖርቶችን ይፋ ባደረገ ቁጥር ከመንግሥት ተቋማት የሚሰነዘረው ትችት ግን ተቋሙ የሌላ አገር እንጂ የመንግሥት ተቋም ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ለማንሳት የሚጋብዝ ነው ይላሉ አንዳንድ ታዛቢዎች፡፡
ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ሪፖርተር ባወጣው ዘገባ፣ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና በወቅቱ ተቋቁሞ በነበረበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ የሚኒስትሮች ኮሚቴ መካከል ተፈጥሮ የነበረን አለመግባባት በሰፊው መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
በወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ፣ የተወሰኑ አንቀጾች ያስከተሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያሠጋው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማሻሻያ እዲደረግ መጠየቁ አይዘነጋም፡፡
አዋጁ በዜጎች ላይ ኢሰብዓዊ አያያዝ እንዲከሰት ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ነው ያለው ኮሚሽኑ፣ በየጊዜው መግለጫ ማውጣቱ በሚኒስትሮች ኮሚቴ መካከል መከፋትና ቁጣን የፈጠረ እንደነበር ዘገባው ይጠቅሳል፡፡
የኮሚቴው አባል የነበሩና ዛሬም በመንግሥት ከፍተኛ የሥራ አመራርነት ላይ የሚገኙ ሰዎች፣ ኮሚሽኑን በጠንካራ ቃላት ማውገዛቸው ተዘግቧል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን፣ ‹‹በሆነ አመለካከትና ፍላጎት ተሠልፈን ባንሳሳብ›› ማለታቸው ተነግሯል፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ደግሞ፣ ‹‹የሁላችንም ዓላማ የዜጎችን መብት መጠበቅ ስለሆነ መግባባት አለብን፤›› ብለው መናገራቸው ተነግሯል፡፡ ያኔ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አሁን ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ ‹‹ኮሚሽኑ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ተገቢነት የላቸውም፡፡ የመብት ጥሰት ገጥሞናልና እርማት ይደረግ ሳይሆን አንቀጾች እንዲወጡ የሚጠይቁ ናቸው፤›› በማለት አጥብቀው መተቸታቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባላት ስላቀረቡት ቅሬታ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሕይወት ለማዳን የሚወሰድ ዕርምጃ ሕይወት ማጥፋት የለበትም፤›› በማለት ነበር ጠንካራ ምላሽ የሰጡት፡፡
በኢትዮጵያ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ አስፈጻሚዎችም ሆነ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት ነፃና ገለልተኛ ናቸው በሚባሉ ተቋማት ላይ የሚያወጡት ትችትና ተቃውሞ ተደጋግሞ ታይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንደ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ፍርድ ቤት የመሳሰሉ ተቋማት ላይ ሌብነት በዝቷል ብለው በፓርላማ እስከተናገሩበት ጊዜም ሆነ፣ ከዚያ ወዲህ ወሳኝ በሚባሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ትችትና ውንጀላው በርክቶ ይታያል ይላሉ ታዛቢዎች፡፡
ይህ ሁኔታ ደግሞ ወትሮም ቢሆን ነፃና ገለልተኛ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባት ረገድ በብዙ ለምትፈተነዋ ኢትዮጵያ ተጨማሪ እንቅፋት ነው የሚሉ ወገኖች ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ ለኮሮና ወረርሽ ተብሎ የታወጀ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የዜጎችን መብት እንዲጣስ እያደረገ ነው ብሎ መጠየቁ ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ተቃውሞ ያስከተለበት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከዚያ በኋላ ባወጣቸው ሪፖርቶችም ቢሆን ብዙ ውግዘትና ተቃውሞዎችን ሲያስተናግድ ታይቷል፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት ራሱ የሠራውን የዴሞክራሲ ተቋም ራሱ መልሶ ለማፍረስ ፍላጎት ያለው ያስመስለዋል የሚሉ አሉ፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር በኮሮና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቅሬታ ወቅት ለመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ‹‹መስማት የሚፈልጉትን ሳይሆን መስማት የሚገባቸውን እናስረዳቸዋለን፤›› በማለት ነበር መልስ የሰጡት፡፡ የሐሳብ ልዩነትን እንደ ተቃውሞ እንደማይቆጥሩት የተናገሩት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ኮሚሽናቸው በሚያወጣቸው ሪፖርቶች ወደፊትም ቢሆን ተመሳሳይ ልዩነት እንደሚገጥመው በወቅቱ ጠቅሰው ነበር፡፡
ይህ የሐሳብ ልዩነት ተብሎ በኮሚሽነሩ የተገለጸ ተቃውሞ ግን ከዚያ በኋላ ተደጋግሞ ከመከሰቱ በተጨማሪ፣ አንዳንዴ እጅግ በከረረ ሁኔታ ሲንፀባረቅ መታየቱ ለዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ጤናማ ምልክት እንዳልሆነ ነው ብዙዎችን የሚያሠጋው፡፡
ከሰሞኑ የጋምቤላው የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት በክልሉና በተቋሙ መካከል ያስነሳው ውዝግብ፣ የዚሁ ማሳያ ተደርጎ እየተነሳ ይገኛል፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ይበቃል ግዛው ግን፣ ሁኔታውን የሚያጋጥምና አንዱ የሥራ አካል መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
‹‹ተቋሙ ዋና ሥራው በመሠረታዊነት በመንግሥትም ሆነ በማንም ጥፋቶች ሲፈጸሙ ማሳየት ነው፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ይበቃል፣ ይህን ሥራ የሚሠራ ተቋም ደግሞ በየትኛውም ዓለም ቢሆን ተቃውሞ ይገጥመዋል ነው ያሉት፡፡ ‹‹ከጋምቤላ ክልል መንግሥት ጋር መደበኛ የመገናኛና የመነጋገሪያ መንገድ አለን፤›› ያሉት አቶ ይበቃል፣ ከዚህ ውጪ የተለየ ምላሽ እንደሌላቸው በመጥቀስ ነበር ሐሳባቸውን በአጭሩ የቋጩት፡፡
የጋምቤላ ክልል ለሰጠው ጠንካራ መግለጫ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሥራ ኃላፊዎች ምላሽ መስጠት እንደማይፈልጉ አበክረው ተናግረዋል፡፡ በሌሎች አጋጣሚዎችም የገጠሟቸውን ተቃውሞዎች ‹‹የሐሳብ ልዩነቶች›› በማለት አቃለው ሲያልፉ የታዩት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሥራ ኃላፊዎች፣ የጋምቤላ ክልል መግለጫንም በተመለከተ በሚዲያ ምላሽ እንደማይሰጡ ነው የተናገሩት፡፡
የዴሞክራሲ ተቋማትን በተመለከተ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ብዙ ኃላፊነት የተጣለባቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጭምር ጠንካራ ንግግር ሲያሰሙ ተደጋግሞ ቢታይም፣ ተቋማቱ ግን ለእነዚህ ንግግሮች አፀፋ ሲሰጡ አይታይም፡፡ ብዙዎች እነዚህ ተቋማት ላልተገቡ ጫናዎች ምላሽ በመስጠት ገለልተኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ ምኞት ቢያሳድሩም፣ የሚታየው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማቱ ልክ እንደ ሌሎች አገሮች ተቋማት ጠንካራና አይነኬ የሚባሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትንና ኃላፊዎችን በድፍረትና ያለ ይሉኝታ ሲጋፈጡ ማየት የሚፈልጉ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማቱ መንግሥትና አስፈጻሚ አካላትን በሥራችን ጣልቃ አትግቡ ብለው ካልተጋፈጡ በስተቀር፣ በአገሪቱ የሰመረ የተቋማት ግንባታ ሒደት እንደማይፈጠር የሚገምቱ ብዙዎች ናቸው፡፡
የጋምቤላ የሰብዓዊ መብቶች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አቤል አዳነ ሪፖርቱ ሲዘጋጅም ሆነ ሲቀርብ፣ የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሚያወጣቸውን ሪፖርቶች መቃወም መብት ነው፡፡ ዋናው ነገር የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሚሠራቸውን የምርመራና የክትትል ሥራዎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች አሠራር ሥርዓቶችን ተከትሎ መሥራቱ ነው፡፡ በእኛ በኩል በጋምቤላ የሠራነው ሪፖርትም ይህንን ሳያጓድል የተሠራ ነው እንላለን፤›› ሲሉ አቶ አቤል ተናግረዋል፡፡
የጋምቤላው የሰብዓዊ መብቶች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለረዥም ዓመታት የቆየ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ አቤል፣ ብዙ የሪፎርም ሥራ መሠራቱን፣ ለሥራው የሚመጥን የትምህርትና ክህሎት ዝግጅት ያላቸው ሰዎች የተመደቡበት መሆኑንና ሪፖርቱ በአጠናኑም ሆነ በአቀራረቡ የጎደለው ነገር አለመኖሩን ነው ያብራሩት፡፡
‹‹የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከመንግሥት አካላት ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለው፡፡ በሚዲያ ለሚቀርቡ ትችቶች አስተያየት የሚሰጥበት አግባብ የለም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ሪፖርቱ የተለያዩ አካላትን በማካተትና ተገቢውን ሒደት ተከትሎ የቀረበ መሆኑን ነው ያሰመሩበት፡፡
ፖለቲካ,ኦነግ ሸኔ,ዓብይ አህመድ ,የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን,ጋምቤላ,ጋነግ,ግጭት