የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሕግ፣ ኹለተኛ ዲግሪያቸውን በሰብዓዊ መብቶች ከደቡብ አፍሪካው ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከቤልጂየሙ ግሄንት ዩኒቨርሲቲ በሰብዓዊ መብቶች አግኝተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት መምህርና ተመራማሪ ነበሩ። አብዲ ጂብሪል (ዶ/ር) አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኹለት ዘርፎችን በኮሚሽነርነት እየመሩ ነው።
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ኮሚሽነር አብዲ ስለ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ መንስኤዎችና ስለ መንግሥት ኃላፊነትና ተያያዥ ጉዳዮች ከአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።
የሲቪልና ፖለቲካ እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ምንድን ናቸው?
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የመብቶች ክፍፍል የታወቀ ነው። ብዙ ጊዜ የተለመደው የኹለቱ የሲቪልና የኢኮኖሚ እና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ነው። በአጠቀላይ ሰብዓዊ መብቶች አይነጣጠሉም፣ አንዱ አንዱ ላይ ይደገፋል። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ አንዱ ሲጣስ ሌላው ይጣሳል የሚል ግንዛቤ አለ።
አንዳንድ አገሮች ለእነዚህ መብቶች ብዙም ትኩረት አይሰጧቸውም። በእኛም አገር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ብዙም ትኩረት አልተሰጣቸውም። ግን ብዙ ጊዜ የቱ ነው ማኅበራዊ፣ የቱ ነው ኢኮኖሚያዊ የሚሉትን ለመለየት ለሰብዓዊ መብቶች ተመራማሪዎችና ለተማሪዎችም ግልጽ አይደሉም።
ብዙውን ጊዜ ሲቪል የምንላቸው መብቶች ለመኖር ብቻ የሚያስፈልጉ ናቸው። እንግዲህ ሰብዓዊ መብቶች ከሰብዓዊነት የሚመነጩ ሰው በመሆን ብቻ የሚገኙ ናቸው። ለምሳሌ፣ አንተ እኔ ጋር ለመምጣት ተንቀሳቅሰህ ነው። ስለዚህ የመንቀሳቀስ መብት ሲቪል የምንለው ሰብዓዊ መብት ዓይነት ነው። ተራ ኑሮ ለመኖር የሚያስፈልጉንን ሲቪል መብቶች እንላቸዋለን።
ፖለቲካ የምንላቸው ደግሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችሉትን ነው። ለምሳሌ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ መረጃ የማግኘት መብት፣ የመደራጀት መብት፣ የመሰብሰብ መብት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብቶች ብዙውን ጊዜ የፖለቲካ መብቶች ብለን ነው የምንወስዳቸው።
ኢኮኖሚያዊ መብቶች የምንላቸው፣ ብዙውን ጊዜ ኑሮ ለመኖር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን ነው። አንደኛው ንብረትን በተመለከተ ነው። ብዙ ጊዜ ንብረት የማፍራትና የመሥራት መብት ከሌለህ በድጋፍ ነው የምትኖረው፣ ያ ድጋፍ ከተቋም ሊሆን ይችላል፣ ከግለሰብ ሊሆን ይችላል።
መጠለያ የማግኘት መብት፣ የመማር መብት፣ ምግብ የማግኘት መብትና የጤና መብት ማኅበራዊ መብቶች እንላቸዋለን። እነዚህ መብቶች ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ለማግኘት የሚጠቅሙ ናቸው።
እነዚህ መብቶች በኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተከበሩ ነው ማለት ይቻላል?
በነገራችን ላይ ብዙውን ጊዜ የሰብዓዊ መብት መከበርን የምንጠይቀው ከመንግሥት ነው። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ይሁን በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን ጣሰ የምንለው ብዙውን ጊዜ መንግሥትን ነው። እንግዲህ መንግሥት ምን ዓይነት ግዴታ አለበት ስንል፣ የማክበርና የማስከበር ግዴታዎችን እንለያለን።
ማክበር ስንል ለምሳሌ ገበሬ ሊሆን ይችላል የገበሬውን ሰብል ቢያቃጥል መንግሥት የማክበር ግዴታውን ነው የሚጥሰው። ያ ገበሬ ከመንግሥት እርዳታ አልፈለገም። ገበሬ ነው፣ እርሻውን አርሶ እየኖረ ነው። ስለዚህ የመንግሥት የምንለው የጸጥታ ኃይል ሄዶ የሚያቃጥል ከሆነ የማክበር ግዴታውን ጥሷል ማለት ነው።
አንተ ወደ እኔ እየመጣህ መንግሥት የሚይዝህና የሚያስርህ ከሆነ፣ ያንተን የነጻነት መብት አላከበረም ማለት ነው። በእርግጥ ሰው አይታሰርም ማለት አይደለም። ሰብዓዊ መብቶች ፍጹም ናቸው ማለት አንችልም፣ የራሳቸው የሚገደቡበት ሁኔታ አለ። ይሄ ግን በሕግ በተቀመጠ አሰራር መሆን አለበት።
መንግሥት ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር ብቻ ሳይሆን የማስከበር ግዴታም አለበት። ማስከበር ስንል ሦስተኛ ወገን የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጥሱ ማስከበር ማለት ነው። እንግዲህ ሦስተኛ ወገን ስንል የታጠቁ ቡድኖች ሊሆኑ ይችላሉ ወይ ደግሞ የንግድ ድርጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ፣ ሦስተኛ ወገኖች የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች እንዳይጥሱ መንግሥት ማስከበር አለበት ማለት ነው።
በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት የሰብዓዊ መብቶችን እያከበረና እያስከበረ ነው ማለት ይቻላል?
አይደለም! በኢትዮጵያም በሌላው ዓለምም አይደለም። ብዙውን ጊዜ የሰብዓዊ መብት ሙሉ በሙሉ ይከበራል ማለት አይቻልም። እኛ አገር ደግሞ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው። በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሰፊ ናቸው። አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው።
ሁሉም የሰብዓዊ መብቶች ተሳክተዋል ወይም ተከብረዋል ማለት ራስን መሸወድ ነው የሚሆነው። ብዙ እርምጃዎች ይቀሩናል። በጣም አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ በተለይ በአገራችን በታጠቀ ቡድንና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሕይወት የመኖር መብት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው ያለው።
ለምሳሌ፣ የሰሜኑን የአገራችንን ሁኔታ ከወሰድነው፣ በታጠቀ ቡድን ነው ያ ሁላ ሕይወት የጠፋው። እኛም በሪፖርታችን ገልጸናል። በግጭቱ ውስጥ ወይም በጦርነቱ ምንም ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች ሞተዋል። አሁን ይሄ በሕይወት የመኖር መብት ጥሰት ስለመሆኑ ምንም የሚያጠያይቅ ነገር የለም። ሶማሌና ኦሮሚያ ክልልን ብንወስድ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ምንም የማያውቁ ሰዎች ተገድለዋል። መንግሥት ሰብዓዊ መብቶች የማክበር ግዴታውን ባለመወጣቱና የማስከበር ግዴታውን መወጣት ባለመቻሉ የሰብዓዊ መብቶች ተፈጽመዋል።
በኦሮሚያ ክልል ሰዎች የሚገደሉት በታጠቀ ቡድን ነው። መንግሥት በመርህ ደረጃ ያንን የታጠቀ ቡድን ተቆጣጥሮ የዜጎችን ደንነት የማስከበር ግዴታ አለበት። ያንን ማድረግ ይችላል ወይ? አቅሙ አለው? የሚለው ሌላ ነገር ሆኖ። መንግሥት እነዚያን የታጠቁ ሰዎች ይዞ በሕግ ተጠያቂ ካለደረገ በሕይወት የመኖር መብት እየተከበረ አይደለም ማለት ነው። በሕይወት የመኖር መብት ከተጣሰ ሌሎች መብቶች ይጣሳሉ።
ምንም ደግሞ አልተከበረም ማለት አይቻልም። በፍጹም ሰብዓዊ መብቶች አልተከበሩም ማለት አይቻልም። ለምሳሌ በድርቅ ለተጎዱ ሰዎችና ለተፈናቀሉ ሰዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሲደረግ እናያለን። ስለዚህ ጥረቶች አናያለን። በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ኹለት ሁኔታዎች አሉ። አንዱ ሰብዓዊ መብቶችን እውን ማድረግ አለመቻል፣ ኹለተኛው ደግሞ ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር አለመፈለግ ናቸው።
ብዙውን ጊዜ በአገራችን ያለው ችግር የአቅም ችግር ነው። አሁን ለምሳሌ መንግሥት ምግብና መጠለያ ማቅረብ ላይ የቻለውን አድርጓል ግን በቂ አይደለም። ይሄ የአቅም ጉዳይ ነው። የታጣቂ ቡድኑን ካየነው ዘመቻ ሲደረጉ፣ ታጣቂዎች ሲያዙ እናያለን። ስለዚህ መንግሥት እጁን አጣጥፎ ቁጭ ብሏል የሚል እምነት የለንም። ሙሉ በሙሉ ችሏል ወይ የሚለውን ስታየው የአቅም ጉዳይ ነው የሚመስለው።
በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዋና መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው?
ስር ለሰደዱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት የሚሆኑና አጣዳፊ የምንላቸው የተለያዩ መንስኤዎች አሉ። ዋናው ችግሩ የእኛን የፖለቲካ ባህል፣ የሰው ግንዛቤ ካየኸው እንደ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መንስኤ ማየት ይቻላል። አሁን ለምሳሌ ሰዎችን የሚገድለው የታጠቀ ቡድን የማኅበረሰቡ አካል ነው፣ ግን ለምንድን ነው ሰዎችን የሚገድለው የሚለውን ካየህ ሰውን የሚገድልበት ምንም አይነት ምክንያት የለም። ሌሎች አገሮችም የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለማሳካት ይጣላሉ፣ እኛ ግን ለምንድን ነው የምንገዳደለው? ካልክ የባህልና የፖለቲካ ባህሉን ልትወስደው ትችላለህ ማለት ነው።
አንድ ሰው የፖለቲካ ሥልጣን የሚይዘው ብዙን ጊዜ በኃይል ነው። ይሄ አንዱ ትልቅ ችግር ነው። ወደፊትም በቀላሉ መፍትሔ ያገኛል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። የፖለቲካ ባህሉን ካየኸው በምክክርና በዴሞክራሲ የተቃኘ አይደለም።
የሞራል ጉዳይ ሌላ መንስኤ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አማኝ ነው ይባላል፣ አማኝ ከሆነ ሌላ ሰው የምትገድልበት ምንም ምክንያት የለም። የሕብረተሰቡን የሞራል መላሸቅ ነው የሚያሳየው። ይሄ ደግሞ ለሰብዓዊ መብት መጣስ አንድ ምክንያት አድርገህ ልትወስደው ትችላላህ።
አንድ ሰው ለምንድን ነው የሰውን ንብረት የሚዘርፈው? የሚያቃጥለው? የሚደፍረው? በየትኛው የሀይማኖት ሞራል ልዕልና ነው የሚፈቀደው? የሚለውን ካየኸው የመጨረሻ የሞራል ዝቅጠት ደረጃን ነው የሚያሳየው። በየትኛውም መስፈርት ጠመንጃ ይዘህ የ15 ቀን ሕጻን የምትገድልበት፣ የሰዎችን ንብረት የምታቃጥልበት ምክንያት የለም።
የኢኮኖሚ ጉዳዮችን አንዱ መንስኤ አድርጎ ማየት ይቻላል። ወጣቶች ሥራ አጥ ባይሆኑ ወደ ጥፋት አይገቡም ማለት የሚቻልበት ሁኔታ አለ። በፖለቲካ በኩል ሲታይ ፖለቲካዊ መንስኤዎች አሉ። ለምሳሌ በደቡብ ክልል በአስተዳደር ጥያቄዎች ብዙ ችግሮች ያጋጥማሉ፣ ከላይ ሲታይ የአስተዳደር ጥያቄ ይመስላል ውስጡ የፖለቲካ ፍላጎት አለው። የአስተዳደር ጥያቄ በሚገባ መልኩ ከተጠየቁ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አያጋጥምም ማለት ነው።
ከታጠቁ ቡድኖች ጋር በተገናኘ ያለው ችግር፣ ችግሮችን በፖለቲካ ውሳኔ መፍታት አለመቻል ነው። ትልቅ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው። መንግሥትን ከታጠቀ ቡድን ጋር አወዳድረህ ተመሳሳይ የሆነ የሞራል ልዕልና ልትሰጠው አትችልም። ያኛው ቡድን ስላላጠፋ ሳይሆን መንግሥት የተሻለ ኃላፊነት አለበት።
በኢትዮጵያ በተለይ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተዋናዮቹ እነማን ናቸው ማለት ይቻላል?
እንግዲህ ቅድም እንዳልኩህ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም ማንም ቢያጠፋ ተጠያቂ የምታደርገው መንግሥትን ነው። መንግሥት ራሱ ያጥፋ፣ ሌላ ቡድን ያጥፋ ተጠያቂ የምታደርገው መንግሥትን ነው። ለምሳሌ በሕይወት የመኖር መብትን ካየን፣ አንደኛ በሕይወት የመኖር መብት የሚጣሰው በግድያ ነው። ኹለት በርሃብ ሊጠፋ ይችላል፣ ሦስተኛ በጤና ሊጠፋ ይችላል። ስለዚህ ለሁሉም መፍትሔ የመፈለጉ ኃላፊነት ያለው መንግሥት ጋር ነው።
በበሽታ ምክንያት የሚጠፋውን ሰው ሕይወት ለማዳን መሰረተ ልማቶችን ማሟላት፣ መድኃኒት ማቅረብ የመሳሰሉ አስፈላጊ ነገሮችን መንግሥት ማቅረብ አለበት ማለት ነው። የሰው ሕይወት በርሃብም ጠፋ፣ በጥይትም ጠፋ፣ በበሽታ ጠፋ መንግሥት በሕይወት የመኖር መብትን ማስጠበቅ አለበት።
የቱ ነው ተዋናይ? ተዋናይ ያልሆነው የቱ ነው? ድርቅ አለ፣ በሽታው አለ፣ ታጣቂ ቡድኑ አለ፣ ሰውን የሚገድል። ሹፌሩ አለ፣ በአግባቡ ሳይነዳ ሕይወት የሚያጠፋ። ግን ዋና ኃላፊነቱ የሚወድቀው መንግሥት ላይ ነው። ለምንድን ነው ታጣቂ ቡድንን ያልተቆጣጠረው? ለምንድን ነው ሕክምና የማያቀርበው? ለምንድን ነው ድርቅ ሲከሰት መስኖ ያላለማው? የሚለውን ስታነሳ ዞሮ ዞሮ መንግሥት ጋር ይደርሳል።
መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ችላ ብሏል የሚሉ ትችቶች ከማኅበረሰቡ እስከ ሰብዓዊ መብት ተቋማትና ተማጋቾች በተደጋጋሚ ይነሳል። ከሰብዓዊ መብት አንጻር መንግሥት ኃላፊነቱን ተወጥቷል ማለት ይቻላል?
አልተወጣም! የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም ይሁን፣ ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ሁሉ መንግሥት ኃላፊነቱን አልተወጣም እንላለን። ቅድም እንዳልኩህ በአቅም ማነስና ባለመፈለግ ሊሆን ይችላል። እኛ መንግሥት ኃላፊነቱን አልተወጣም እያልን ነው። መንግሥትም ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ ይላል ብዬ አላስብም።
ለምሳሌ ምዕራብ ኦሮሚያ የጸጥታ ችግር አለ። የጸጥታ ችግር መኖሩ መንግሥት ኃላፊነቱን አለመወጣቱን ነው የሚያሳየው። የተራበ ሰው እስካለ ድረስ፣ በበሽታ የሚሞት ሰው አስካለ ድረስ መንግሥት ኃላፊነቱን ተወጥቷል ማለት አይቻልም። በከፊል ኃላፊነቱን ተወጥቷል ሊባል ይችላል እንጂ ሙሉ ነው ማለት አይቻልም።
የፌዴራል መንግሥት እና የክልል መንግሥታት ኢሰመኮ በየጊዜው የሚያቀርባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራና ምክረ ሐሳቦች ተቀብለው ተግባራዊ የማድረግ ፍላጎታቸው እንዴት ነው?
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ ይደረጋሉ ለሚለው ጥያቄ መልሱ አዎም ነው፣ አይደለምም ነው። ምክረ ሐሳቦቻችንን ካየን ወዲያውኑ ሊተገበሩ የሚገባቸውና የተተገበሩ ምክረ ሐሳቦች አሉ። ጊዜ የሚፈጁ ምክረ ሐሳቦች አሉ። አቅም የሚጠይቁ ምክር ሐሳቦች አሉ።
ለምሳሌ በሰሜኑ ጦርነት የተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መሰረት አድርገን ባቀረብነው ምክረ ሐሳብ መንግሥት ግብረ ኃይል አቋቁሞ ምርመራ እያደረገ ነው። ስለዚህ ምክረ ሐሳቦቻችንን ሙሉ በሙሉ አይቀበልም ማለት አንችልም። የምናቀርባቸው ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ ሆነዋል አልሆኑም የሚሉትን እንከታተላለን።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ ካልተደረጉ፣ ለምንድን ነው ኮሚሽኑ የሚኖረው? በመንግሥትም ደረጃ በሕዝብም የኮሚሽኑ ምክረ ሐሳቦች ካልተተገበሩ የኮሚሽኑ መኖር አስፈላጊ አይደለም ማለት ነው። ግን እኛ የምንሰጠውን ምክረ ሐሳብ መንግሥት የመፈጸም አቅም አለው ወይ? የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው። ለምሳሌ በሰሜኑ ጦርነት የወደሙ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት መልሰው እንዲቋቋሙ ምክረ ሐሳብ አቅርበናል። ግን መንግሥት ይችላል ወይ? አቅም አለው ወይ የሚለው ጉዳይ የአቅም ውስነት ነው።
መንግሥት የታጠቁ ኃይሎችን የመደምሰስ አቅም አለኝ እያለ በየጊዜው በሚገልጽበት ሁኔታ እርስዎ እንደሚሉት የሰብዓዊ መብቶችን የማያስከብረው የአቅም ማነስ ስላለበት ነው ማለት ይቻላል ማለት ነው?
እንግዲህ ውሳኔውን ለአንተው እተዋለሁ። ምክንያቱም መቆጣጠር ከቻለ መሰረታዊ የመንግሥት ፍላጎት ነው ብዬ ነው የማስበው። እኔን እንደ ግለሰብ ከጠየከኝ፣ የትኛውንም የታጠቀ ቡድን ለማንበርከክ የሰው ኃይል፣ የመሳሪያ አቅርቦት ይጠይቃል።
እኔ እንደማስበው ይሄን ማድረግ አቅም እንደሚፈልግ ነው። የትኛውም ሰብዓዊ መብቶችን ለማሳካት ትልቅ ሀብት ነው የሚጠይቀው። ያለን አቅም በየትኛውም ሁኔታ ብትወስደው የተገደበ ነው። ግን የትኛውም የታጠቀ ኃይል ከመከላከያ አቅም በላይ ነው የሚል ግምት የለኝም።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አሁንም እንደቀጠሉ ከመሆናቸው አንጻር፣ ሙሉ በሙሉ ማስቆም ባይቻልም እንኳን ማሻሻል ወይም እንዳይባባስ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
መንስኤውን ከለየን መፍትሔው ቀላል ነው። ግን ማድረግ መቻሉ ነው የሚቸግረው። በጠመንጃ የሚያምን ፖለቲከኛ ይዘህ ሁሉንም ነገሮች በውይይትና በጠረጴዛ ዙሪያ እፈታለሁ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ በመሰረታዊነት የሰዎችን አስተሳሰብ መቀየር አስፈላጊ ነው። ሰብዓዊ መብት ስንል ስለ ሰው ልጅ እንጂ ስለ አንድ ጉዳይ አይደለም።
የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች እንደመኖራቸው ሁሉንም ማስከበር ካልተቻለ አንዱ አንዱ ላይ ስለሚመሰረት አንዱ ከተጣሰ ሌላው መጣሱ አይቀርም። አንድ ሰው በልቶ ማደር ካልቻለ መሞቱ ነው እና የሲቪል መብቱ ሲጣስ በሕይወት የመኖር መብቱ ይጣሳል። ስለዚህ ለሁሉም ሰብዓዊ መብቶች መከበር መፍትሔ መፈለጉ አስፈላጊ ነው ብዬ ነው የማስበው።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲያጣራ ያቋቋመው ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ኮሚሽን፣ መንግሥት የገለልተኝነት ጥያቄ በማንሳት አልተባበርም ሲል ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ላይ መንግሥት ምርመራ እንዲደረግ ስምምነት ላይ ደርሷል፣ የተሰየመው ኮሚሽን ምርመራ ማድረጉን እንዴት ይመለከቱታል?
ኹለት ነገር መለየት ያስፈልጋል። አንደኛ ፖለቲካዊ ምክንያቱን መለየቱ፣ ውሳኔውን የአፍሪካ አገራት አልደገፉትም ነበር። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መንግሥት አልቀበልም ማለቱ አይደንቅም። የተሰየመው የባለሙያዎች ቡድን ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ የተደረገውን ምርምራ የሚደግም ከሆነ፣ አንደኛ ማሰልቸት ነው። ኹለተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መከሰታቸው በምርመራ ተረጋግጧል። ስለዚህም በምርመራው መሰረት መፍትሔ መፈለግ ነው እንጂ ሌላ ምርመራ ማድረጉ በተለይ ለተጎጂዎቹ ይሄን ያክል ጠቃሚ ሆኖ አይታየኝም።
በተደረገው ምርምራ መሰረት መፍትሔ በመፈለግ ፋንታ፣ ወደኋላ ተመልሶ ሌላ ምርመራ ማድረግ መፍትሔ ይዘግይ እንደማለት ነው። በጋራ የተደረገው ምርመራ ወካይ ነው ብለን ነው የምናስበው። የኢትዮጵያ መንግሥት አልቀበልም ማለቱ የፖለቲካ ውሳኔ ነው የወሰነው፣ እንደገና መፍቀዱ ብዙ ችግር ያለው አይመስለኝም።
ቅጽ 4 ቁጥር 198 ነሐሴ 14 2014